Thursday, February 22, 2024

 

ያልተጠየቀ ዳኝነት አይሰጥም፤ በግልጽ ያልተሰጠ ፍርድም አይፈጸምም።

መሰረታዊው የፍትሐብሔር ክርክር አመራር መርህ በግልጽ ያልተጠየቀ ዳኝነት አይሰጥም የሚል ነው። ይህም ስለፍርድ በሚያትተው የፍትሀብሄር ሥነ-ሥርዓት ህጉ ክፍል በቁጥር 182/2/ ስር በግልጽ ተደንግጓል። ፍርድና ውሳኔ በዚህ መርህ መሰረት በጥብቅ ሥርዓት ከተሰጠ በኋላ ፍርድ አስፈጻሚው እንደፈለገው ከፍርዱ ይዘት እየወጣ የሚወስንና የሚያስፈጽም ከሆነ ያልተጠየቀ ዳኝነት እንደመስጠት የሚቆጠር በመሆኑ ይህን መርህ የሚቃረን ነው።
በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ህግ ከቁጥር 371 ጀምሮ የተመለከቱት የፍርድ አፈጻጸምን የሚመሩት ድንጋጌዎች በተደጋጋሚ ‘እንደፍርዱ የሚያስፈጽመው’ የሚል ሀረግ ያዘሉ ናቸው። እንደፍርዱ የሚለው የዚህ ሀረግ ቃልም በአፈጻጸም ወቅት ከፍርድና ከውሳኔ ላይ መቀነስም ሆነ መጨመር እንደማይቻል የሚያስረግጥ ነው።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 80/3/ሀ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የሚሰጣቸው ውሳኔዎች በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ ፍርድ ቤቶችን የሚያስገድዱ ናቸው። ችሎቱ በሰ/መቁጥር 152172 (ቅጽ 23)፥ 29949 (ቅጽ 6)፥ 103787 (ቅጽ 19)፥ 28019 እና 29344 (ቅጽ 7)፥ 50148 (ቅጽ 9)፥ 96814 (ቅጽ 18) እና በሌሎችም መዛግብት በተሰጡ የህግ ትርጉሞች አንድ ሰው በአፈጻጸም ሊገደድ የሚችለው በህግ አግባብ የተፈረደ ፍርድ ሲኖር ብቻ ስለመሆኑ፤ ግልጽ ፍርድ ያላረፈበት ጉዳይ ሊፈጸም እንደማይችል፤ አፈጻጸም ችሎቶች ስለፍርድ አፈጻጸም የተዘረጉትን ሥርዓቶች በመከተል እንደፍርዱ ከማስፈጸም በቀር የአንድን ፍርድ ይዘት አድማስ ማጥበብም ሆነ ማስፋት እንደማይችሉ፤ አንድ የፍርድ አፈጻጸም ክስ ማመልከቻ ይፈጸም የተባለውን ፍርድ ብቻ መሰረት ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ አሰገዳጅ ትርጉም ሰጥቷል።
ያልተጠየቀ ዳኝነት አይሰጥም፥ ያልተሰጠ ፍርድ አይፈጸምም የሚለው መሪ ህግ የፍትሀብሄር ሥነ-ሥርዓት ህግ ዋነኛ መርህ የሆነውም ህገ-መንግስታዊ የሆኑ እና በዓለም አቀፍ የሰብዐዊ መብት የቃል ኪዳን ሰነዶች የተረጋገጡ መሰረታዊ እና ሥነ-ሥርዓታዊ መብቶችን/Substantive and Procedural Rights/ ለማክበር እና ለማስከበር ነው። ተከሳሾች የሚቀርብባቸውን ማናቸውንም ክስ አስቀድመው የማወቅ፥ የመቃወም፥ የመከራከር፥ የመደመጥና ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን ማስረጃዎች አቅርበው የማስተባበልና ፍትህ የማግኘት መብት እንዳላቸው (የሥነ-ሥርዓት መብቶች-Due Process Rights) በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 20 እና 37 እንዲሁም በዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን አንቀጽ 14 ተደንግጓል። የህገመንግሰቱ አንቀጽ 40 ም የአንድ ሰው ንብረት ተገቢውን የሥነ-ሥርዓት ሂደት ሳይከተል ሊወሰድበት/ሊተላለፍ እንደማይችል የሚያዝዝ ነው።
 
ጠበቃ እና የህግ አማካሪ እንዳላማው አለልኝ/0912771896/

 

በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁጥር 213/92 መሰረት ከጋብቻ ውጭ እንደባልና ሚስት ስለመኖሩ የሚቀርብ ማስረጃ
ከጋብቻ ውጭ እንደባልና ሚስት መኖር ሴቲቱ እና ወንዱ ጋብቻ ሳይፈጽሙ በጋራ እንደባልና ሚስት መኖር በመጀመራቸው ብቻ የሚመሰረት ነው።
ይህን ግንኙነት ማስረዳት የሚቻለውም በአንቀጽ 106 /1/ እና /2/ እንደተመለከተው የግንኙነቱን መኖር በማስረዳት ሲሆን ይህ ግንኙነት አለ የሚባለውም ሁለቱ በህግ የተጋቡ ባይሆንም የተጋቡ ሰዎችን ሁኔታ የሚያሳዩና በቤተዘመድ እና በማህበረሰቡም እንደተጋቡ ሰዎች የሚኖሩ ናቸው ተብለው ሲገመቱ ነው። ይህ ማስረጃ ከቀረበም እንደባልና ሚስት አብረው የሚኖሩ ናቸው ተብሎ የህግ ግምት የሚወሰድ ሲሆን ግምቱንም ግንኙነቱ አለመኖሩን ማስረጃ አቅርቦ በማስረዳት ማስተባበልና ማፍረስ ይቻላል።
በሰበር መዝገብ ቁጥሮች 50580/ቅጽ 11/፥ 96853/ቅጽ 18/፥ 126411/ቅጽ 22/ የተሰጡ ትርጉሞቸን ለበለጠ ግንዛቤ ማንበብ ይችላሉ።
Endalamaw Alelign/LLM, LLB/
Attorney and Legal Consultat
0912771896
የጋብቻ ውል/የተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁጥር 213/92 ከአንቀጽ 42-48/
የጋብቻ ውል ልዩ ከሚባሉት የውል አይነቶች አንዱ ነው። የውሉ ዓላማም ተጋቢዎቹ ስለጋራ እና የግል ንብረታቸው እና ስለአስተዳደሩ ሁኔታ እንዲሁም ስለግል ግንኙነታቸውና ስለቤተሰብ አስተዳደር ስምምነት የሚያደርጉበት ነው። ውሉ የሚደረገውም ከጋብቻ መፈጸም በፊት ወይም እጅግ ቢዘገይ ጋብቻ በሚፈጸምበት ቀን ነው። እንደማናቸውም ውል ሁሉ ውሉ ከሞራልና ከህግ ተቃራኒ መሆን አይችልም። ተጋቢዎቹም በፈቃዳቸው ስምምነት ሊያደርጉበት ይገባል። በፎርም ደረጃ ውሉ በ4 ምስክሮች ሊረጋገጥ የሚገባ ሲሆን ሁለት በባል ወገን ሁለት በሚስት ወገን የሚጠሩ ናቸው። ፎርሙን ያልጠበቀ ውልም ተቀባይነት አይኖረውም።
ሥርዓቱን ጠብቆ የተደረገ ህጋዊ የጋብቻ ውል በጋብቻ ወቅትም ሆነ በፍቺ ጊዜ/የፍቺ ውጤቶችን ለመወሰን/ የሁለቱን ተጋቢዎች ግንኙነት የሚገዛ ህግ ይሆናል። በቤተሰብ ህጉ ከአንቀጽ 49 ጀምሮ የተመለከቱት ድንጋጌዎች የሚተገበሩትም እንዲህ አይነት ተቀባይነት ያለው ውል በሌለ ጊዜ ነው (አንቀጽ 48 እና የፍ/ህግ ቁጥር 1676 እና 1731)።
ጋብቻ ከተፈጸመ በኋላ የጋብቻ ውሉን ለማሻሻል ይቻላል። ነገር ግን በጋብቻ ወቅት የጋብቻ ውል ለማሻሻል የሚደረግ ስምምነት ፍርድ ቤት ቀርቦ ካልጸደቀ በቀር በህግ ፊት ዋጋ የለውም። የዚህ የፍርድ ቤቶች ጣልቃ-ገብነት ያስፈለገውም በመደራደር ዐቅሙ የተሻለው ተጋቢ ደካማውን ወይም በቀላሉ የሚያምነውን ተጋቢ አሳምኖ መብቱን የሚጎዳ ስምምነት እንዳያደርግ ለመከላከልና የእርሱንና የቤተሰቡን መብትና ጥቅም ለመጠበቅ ነው።
 Endalamaw Alelign Menge/LLM, LLB/
Attorney and Legal Consultant

 

  ያልተጠየቀ ዳኝነት አይሰጥም፤ በግልጽ ያልተሰጠ ፍርድም አይፈጸምም። መሰረታዊው የፍትሐብሔር ክርክር አመራር መርህ በግልጽ ያልተጠየቀ ዳኝነት አይሰጥም የሚል ነው። ይህም ስለፍርድ በሚያትተው የፍትሀብሄር ሥነ-ሥርዓት ህጉ...