የጋብቻ ውል/የተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁጥር 213/92 ከአንቀጽ 42-48/
የጋብቻ ውል ልዩ ከሚባሉት የውል አይነቶች አንዱ ነው። የውሉ ዓላማም ተጋቢዎቹ ስለጋራ እና የግል ንብረታቸው እና ስለአስተዳደሩ ሁኔታ እንዲሁም ስለግል ግንኙነታቸውና ስለቤተሰብ አስተዳደር ስምምነት የሚያደርጉበት ነው። ውሉ የሚደረገውም ከጋብቻ መፈጸም በፊት ወይም እጅግ ቢዘገይ ጋብቻ በሚፈጸምበት ቀን ነው። እንደማናቸውም ውል ሁሉ ውሉ ከሞራልና ከህግ ተቃራኒ መሆን አይችልም። ተጋቢዎቹም በፈቃዳቸው ስምምነት ሊያደርጉበት ይገባል። በፎርም ደረጃ ውሉ በ4 ምስክሮች ሊረጋገጥ የሚገባ ሲሆን ሁለት በባል ወገን ሁለት በሚስት ወገን የሚጠሩ ናቸው። ፎርሙን ያልጠበቀ ውልም ተቀባይነት አይኖረውም።
ሥርዓቱን ጠብቆ የተደረገ ህጋዊ የጋብቻ ውል በጋብቻ ወቅትም ሆነ በፍቺ ጊዜ/የፍቺ ውጤቶችን ለመወሰን/ የሁለቱን ተጋቢዎች ግንኙነት የሚገዛ ህግ ይሆናል። በቤተሰብ ህጉ ከአንቀጽ 49 ጀምሮ የተመለከቱት ድንጋጌዎች የሚተገበሩትም እንዲህ አይነት ተቀባይነት ያለው ውል በሌለ ጊዜ ነው (አንቀጽ 48 እና የፍ/ህግ ቁጥር 1676 እና 1731)።
ጋብቻ ከተፈጸመ በኋላ የጋብቻ ውሉን ለማሻሻል ይቻላል። ነገር ግን በጋብቻ ወቅት የጋብቻ ውል ለማሻሻል የሚደረግ ስምምነት ፍርድ ቤት ቀርቦ ካልጸደቀ በቀር በህግ ፊት ዋጋ የለውም። የዚህ የፍርድ ቤቶች ጣልቃ-ገብነት ያስፈለገውም በመደራደር ዐቅሙ የተሻለው ተጋቢ ደካማውን ወይም በቀላሉ የሚያምነውን ተጋቢ አሳምኖ መብቱን የሚጎዳ ስምምነት እንዳያደርግ ለመከላከልና የእርሱንና የቤተሰቡን መብትና ጥቅም ለመጠበቅ ነው።
Endalamaw Alelign Menge/LLM, LLB/
Attorney and Legal Consultant
No comments:
Post a Comment